ትዳርና የቤተሰብ ኑሮ

 

ለኦርቶዶክስ ጋብቻ መመሪያ

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰባት ስብከቶች ስለ ወንድ እና ሴት፡የትዳር ሕይወትና የትዳር ላይ ጥቃት)

4.  የጥናት ዘዴ


ይህ ጥናት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በትዳር ዙሪያ የጻፋቸውን ስብከቶች በጥንቃቄ በማንበብ እና በመመርመር የተዘጋጀ ነው፡፡ የዚህ ጥናት ጸሐፊ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ሀያ የተለያዩ ስብከቶች በተጻፉበት ጥንታዊ ግሪክ ቋንቋ ያነበበች ሲሆን ከእነርሱ መካከል ሰባቱ በዚህ ጥናት ላይ ተጠቅሰዋል፡፡[1] ትኩረት ሊሰጣቸው የተገቡት ስብከቶች የተመረጡትም፡ ሀ) የትዳር ግንኙነትን በተመለከተ ከመጽሐፍ ቅዱስ (በተለይ ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት) የተውጣጡ ጥቅሶች እና ለ) በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥራ ላይ በእንግሊዝኛ ወይም በግሪክ ቋንቋ የተጻፉ ምንጮች በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ጥናት እጅግ ጥልቅ ሊባል ባይችልም እንኳ በተመረጡት ርዕሶች ዙሪያ ጠቅለል ያለ ኦርቶዶክሳዊ አረዳድን ለመፍጠር ሙከራ የተደረገበት ነው፡፡

በዚህ ሥራ ላይ የተጠቀሱት የጥንታዊ ግሪክ ምንጮች በቀጥታ በህዳግ ማስታወሻ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ የዚህም ምክንያት መዛግብቱ የተጻፉበት ጥንታዊ ቋንቋ መሠረት በማድረግ ተገቢ የሆነ የትርጓሜ ዐውድ ለማስቀመጥ ስለሚረዳ ነው፡፡ ለዚህ ሥራ እንደ ግብዓትነት የዋሉትን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሥራዎች የተረጎሙት ምንጮች በአብዛኛው ሥራዎቹን ለመተርጎማቸው ምክንያትም ሆነ የተጠቀሙበትን የትርጓሜ መንገድ ግልጽ አላደረጉም፡፡ ሆኖም ግን የግሪክ ቋንቋ ሰፊ የትርጓሜ ዐውድ ከማካተቱ አንጻርና ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ቁልፍ ቃላቶችን በተገቢው ኦርቶዶክሳዊ ዐውድ በማድረግ ብያኔ መስጠታቸውን ታሳቢ በማድረግ[2] በትርጓሜ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡ ሆኖም ግን ካለን ውስን ቦታ አንጻር በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንዲህ ማድረግ አልተቻለም፡፡ የእንግሊዝኛ ትርጉም ያላቸው ሥራዎችን አንባቢ በቀላሉ እንዲያገኛቸው በምንጭነታቸው በቀጥታ ተጠቅሰዋል፡፡ የዚህ ጥናት ጸሐፊ ያስተካከላቸውን እና በህዳግ ማስታወሻ የተጠቀሱት ሥራዎች ግን ጸሐፊውን በመጠየቅ ማግኘት ይቻላል፡፡[3]

በአብዛኞቹ የትርጉም ሥራዎች ላይ ‹ትዳር› ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ‘
γάμος’ [ጋሞስ] የሚለው ነው፡፡ ሆኖም ግን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ቃል በተጠቀመባቸው ቦታዎች ሁሉ ‹ትዳር› ብሎ መተርጎም (በተለይ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ስንናገር) የቃሉን ሰፊ አንድምታ ያኮስሰዋል ምክንያቱም ከጾታዊ ግንኙነት ነጻ ስለሆነው እና በሰማይ ስላለው ኅብረት ሲጽፍ ‘γάμος’ የሚለውን ቃል ጾታዊ መሳሳብ የሌለበትን ግንኙነትም ለመጥቀስ ይጠቀምበታልና ነው፡፡[4] የሰው ልጅ ከገነት ከተባረረ በኋላ ግን ጾታዊ ግንኙነት በትዳር ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶ የሰው ልጅን የድኅነት ጎዳና የሚያሳልጥ ምሥጢራዊ እና መንፈሳዊ ግንኙነት አካል ሆኗል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው ከሆነ እግዚአብሔር የአዳምን ውድቀት ስለሚያውቅ አስቀድሞ በወንድ እና በሴት መካከል ከፍተኛ የሆነ መቀራረብን ፈጥሯል፡፡ ይህም ደግሞ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በትዳር በኩል ለሚገኘው የሰው ልጅ ድኅነት አስተዋጽኦን የሚያደርግ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ትዳር በሚያወራበትም ጊዜ የሚያወራው ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ ስላለው የትዳር ጥምረት ሲሆን፤ ይህም ደግሞ በሰማይ ካለው ጥምረትም ሆነ ከድንግልና ሕይወት የተለየ ነው፡፡

 



[1] እነዚህ ሥራዎች የተገኙት ከኤጊያን ዩኒቨርሲቲ Migne’s Patrologia Graeca ምህዳር ነው፡፡

 

[2] የሚከተለውን ምንጭ ይመልከቱ፡- Panayiotis Nellas, Deification in Christ: Orthodox Perspective on the Nature of the Human Person (New York: St Vladimir’s Press, 1987), 16.

[3] በዚህ ያሉት አንዳንድ የእንግሊዝኛ አንድምታዎች ከእንግሊዝኛ ጸሐፊያን ሥራዎች ላይ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የዚህ ጥናት ጸሐፊ እንደ አስፈላጊነቱ የኦሪጅናሉን ግሪክ ምንጭ በመመልከት ጥቃቅን እና ትላልቅ ለውጦችን አድርጋለች፡፡ እነዚህን ለውጦች ለማየት እንዲያመች ጠመም ባለ ፊደል እንዲሰፍሩ ተደርገዋል፡፡
[4] ይህንን ግልጽ ለማድረግ γάμος የሚለውን ቃል ምንጭ ማየት ነው፡፡ የቃሉ ምንጭ ትርጉም ‹አብሮ መተኛት› (‘γαμέω/γαμώ’) የሚል ነው፡፡

 


ምዕራፍ 3 ወደ ይዘቶች ተመለስ ምዕራፍ 5