መሠረታዊ ኦርቶዶክስ አስተምህሮ

 

የቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮዎች ምርጫ
1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች

ምዕራፍ 4: ምክር እና ወንድማዊ ፍቅር

1 እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን። 
2 በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና። 
3 ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ 
4- 5 ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤ 
6 አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል። 
7 ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። 
8 እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ። 
9 እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤ 
10- 11 እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥
12 በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን። 
13 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። 
14 ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና። 
15 በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤ 
16 ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ 
17 ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። 
18 ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።

 

ምዕራፍ 5: የጌታ ዳግም ምጽአት ድንገት እንደሚደርስ

1 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤ 
2 የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና። 
3 ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም። 
4 እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥ 
5 ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤ 
6 እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ። 
7 የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤ 
8 እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤ 
9 እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ። 
10 የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ። 
11 ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው። 
12-13 ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ። 
14 ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። 
15 ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ። 
16 ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ 
17-18 ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና። 
19 መንፈስን አታጥፉ፤ 
20-21 ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤ 
22 ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ። 
23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። 
24 የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል። 
25 ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ። 
26 ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። 
27 ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ። 
28 የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።