መሠረታዊ ኦርቶዶክስ አስተምህሮ

 

የቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮዎች ምርጫ
 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

ምዕራፍ 8: የመቄዶንያ ቤተክርስቲያን ልግስና

1 ወንድሞች ሆይ፥ ለመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እናስታውቃችኋለን፤ 
2 በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸው ብዛትና የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል፤ 
3 እንደ ዓቅማቸው መጠን ከዓቅማቸውም የሚያልፍ እንኳ ወደው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁና። 
4 ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር፥ 
5 አስቀድመውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለጌታ ለእኛም ሰጡ እንጂ እንዳሰብን አይደለም። 
6 ስለዚህም ቲቶ አስቀድሞ እንደ ጀመረ እንዲሁ ደግሞ ይህን ቸር ሥራ ደግሞ በእናንተ ዘንድ ሊፈጽም ለመንን። 
7 ነገር ግን በነገር ሁሉ፥ በእምነትና በቃል በእውቀትም በትጋትም ሁሉ ለእኛም በፍቅራችሁ እንደ ተረፋችሁ፥ በዚህ ቸር ሥራ ደግሞ ትረፉ። 
8 ትእዛዝ እንደምሰጥ አልልም፥ ነገር ግን በሌሎች ትጋት በኩል የፍቅራችሁን እውነተኛነት ደግሞ ልመረምር እላለሁ፤ 
9 የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ። 
10 በዚህም ነገር ምክር እሰጣለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ ለማድረግ ብቻ ያይደለ ነገር ግን ለማሰብ ደግሞ አስቀድማችሁ የጀመራችሁት ይህ ይጠቅማችኋልና፤ 
11 አሁንም ለማሰብ በጎ ፈቃድ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እንዳላችሁ መጠን መፈጸም ደግሞ ይሆን ዘንድ፥ ማድረጉን ደግሞ ፈጽሙ። 
12 በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም። 
13 ለሌሎች ዕረፍት ለእናንተም መከራ እንዲሆን አይደለም፥ ትክክል እንዲሆን ነው እንጂ፤ 
14 የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ፤ በትክክል እንዲሆን፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። 
15 ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፥ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም። 

 

ምዕራፍ 9: ስለ ቅዱሳን አገልግሎት

1 ለቅዱሳን ስለሚሆነው አገልግሎት ልጽፍላችሁ አያስፈልግምና፤ 
2 በጎ ፈቃዳችሁን አውቄአለሁና፤ ስለዚህም። አካይያ ከአምና ጀምሮ ተዘጋጅቶአል ብዬ ለመቄዶንያ ሰዎች በእናንተ እመካለሁ፥ ቅንዓታችሁም የሚበዙቱን አነሣሥቶአል። 
3 ነገር ግን ለእነርሱ እንዳልሁ፥ የተዘጋጃችሁ ትሆኑ ዘንድ በዚህም ነገር ስለ እናንተ ያለው ትምክህታችን ከንቱ እንዳይሆን ወንድሞችን እልካለሁ፤ 
4 ምናልባት የመቄዶንያ ሰዎች ከእኔ ጋር ቢመጡ፥ ያልተዘጋጃችሁም ሆናችሁ ቢያገኙአችሁ፥ እናንተ እንድታፍሩ አላልንም እኛ ግን በዚህ እምነታችን እንድናፍር አይሁን። 
5 እንግዲህ እንደ በረከት ሆኖ ከስስት የማይሆን ይህ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ አስቀድመው ወደ እናንተ መጥተው፥ አስቀድማችሁ ተስፋ የሰጣችሁትን በረከት አስቀድመው እንዲፈጽሙ ወንድሞችን እለምን ዘንድ እንዲያስፈልገኝ አሰብሁ። 
6 ይህንም እላለሁ። በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ደግሞ ያጭዳል፥ በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል። 
7 እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፥ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም። 
8- 9 በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። 
10 ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ 
11 በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። 
12 የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤ 
13 በዚህ አገልግሎት ስለ ተፈተናችሁ፥ በክርስቶስ ወንጌል በማመናችሁ ስለሚሆን መታዘዝ እነርሱንና ሁሉንም ስለምትረዱበት ልግስና እግዚአብሔርን ያከብራሉ፥ 
14 ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 
15 ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።